በህፃናት መረጃ ድርጅት UNICEF ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ ዕድሜያቸዉ ከ10-19 አመት ለሆኑ ሴት ልጃገረዶች በክልሉ በተመረጡ ት/ቤቶች መሰጠት የተጀመረው ሳምንታዊ የአይሬን ፎሌት/WIFAS/አሰጣጥ የተሻለ መሆኑ ተገለፀ ።
ከወር አበባ መፍሰስ ጋር ተያይዞ በሴት ልጃገረዶች ላይ የደም ማነስ ችግሮች እንዳይከሰቱ በዩኒሴፍ የገንዘብ ድጋፍ በክልሉ በተመረጡ ወረዳዎች ዕድሜያቸው ከ10-19 አመት ለሆኑ ሴት ልጃገረዶች የአይረን ፎሌት እየተሰጠ ይገኛል ።
የእነዚህ ወረዳዎች አፈጻጸም በመገምገም የተሻሉ አሰራሮችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና መሻሻል በሚገባቸው አሰራሮች ላይ በትኩረት ለመስራት የሥራ ግምገማ መድረክ መዘጋጀቱን የአሶሳ ዞን ጤና መመሪያ ሀላፊ አቶ ሙሳ አህመድ ገልጸዋል ።
ከ10-19 አመት ያለዉ ጊዜ ከልጅነት ወደ አዋቂነት የመሸጋገሪያ ወቅት በመሆኑ በዚህ ዕድሜ ክልል ዉስጥ ባሉ አፍላ
ወጣቶች ላይ መሰራት አስፈላጊ በመሆኑ ፕሮግራሙ በክልሉ በተመረጡ ወረዳዎች መጀመሩን አቶ ሙሳ ገልፀዋል።
መምሪያ ሀላፊዉ አክለዉም ፕሮግራሙ ሴቶች ጠንካራ አቅም እንዲኖራቸው፣የአፍላ ወጣት ሴቶች ጤናን እና እድገት የሚያሻሽል በመሆኑ ለፕሮግራሙ መሳካት የሁሉም ርብርብ ወሳኝ ነው ብለዋል።
በዚሁ መሠረት ፕሮግራም ተግበራዊ ለማድረግ በባለፉት 9 ወራት በየት/ቤቶች የተከናወኑ እና የተመዘገቡ ዉጤቶች አበረታች በመሆናቸው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት መምሪያ ሀላፊው ተናግረዋል ።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በፕሮግራሙ ዙሪያ ወቅታዊ መረጃን በወቅቱ ያለማቅረብ እና የቅንጅታዊ አሰራር ክፍተቶች መስተካከል አለባቸዉ ብለዋል።




