የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል ድንገተኛ የህክምና ማዕከል በቅርቡ ሥራ እንደሚጀመር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ።
በአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል በድንገተኛ የህክምና ማዕከል የሚሰጠዉን የህክምና አገልግሎት ለማሻሻል በጤና ሚኒስቴር የገንዘብ ድጋፍ ደረጃውን የጠበቀ የህክምና ማዕከል ተገንብቶ መጠናቀቁ ይታወቃል ።
ይህን ግንባታ ሥራ ለማስጀመር ለህክምና መስጫ አገልግሎት የሚያስፈልጉ የህክምና ቁሳቁሶች የተሟሉ ስለሆነ በቅርብ ቀን ዉስጥ ተመርቆ አገልግሎት እንደሚጀምር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ የፕሮግራም ዘርፍ ምክትል ሀላፊና የአሶሳ አጠቀላይ ሆስፒታል ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብዱልሙኒየም አልበሽር ገልጸዋል ።
ይህ የህክምና ማዕከል የላብራቶሪ፣ የመድኃኒት ክፍል፣የህፃናት እና የአዋቂዎች ተኝቶ ህክምና፣የመለስተኛ ቀዶ ህክምና እና የአልትራሳዉንድ አገልሎቶችን ያያዘ መሆኑን የገለፁት ምክትል ቢሮ ሀላፊዉ የህክምና ማዕከሉ መገንባት በድንገተኛ የህክምና ማዕከል የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ቀልጣፋና ጥራት ያለዉ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።
በአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል የተገነባው የድንገተኛ የህክምና ማዕከል በጤና ሚኒስቴር የገንዘብ ድጋፍ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባ ሲሆን ማዕከሉ ለተለያዩ አገልግሎት የሚዉሉ 16 ክፍሎች እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል፡፡
