በክልሉ ለምግብ ስርዓት ሽግግርና ኒውትሪሽን ፍኖተ-ካርታ ትግበራ ባለድርሻ ተቋማት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ ገለጹ
***
(አሶሳ፣ ሚያዚያ 15/2018 ዓ.ም) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለምግብ ስርዓት ሽግግርና ኒውትሪሽን ፍኖተ-ካርታ ትግበራ ባለድርሻ ተቋማት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ ገለጹ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ ለአምስት ዓመታት የሚተገበር የምግብ ስርዓት ሽግግርና ኒውትሪሽን ፍኖተ-ካርታ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ተካሂዷል።
እንደሀገር የምግብ ስርዓት ሽግግርና ኒውትሪሽን ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቶ በትግበራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ክልሎችም የራሳቸውን ፍኖተ-ካርታ አዘጋጅተው ወደተግባር እንዲገቡ እየተደረገ ነው።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የምግብ ስርዓት ሽግግርና ኒውትሪሽን ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቶ ባለድርሻ ተቋማት አመራሮች እና ፈጻሚዎች በተገኙበት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በመርሐ-ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ እንደገለጹት፣ የምግብ ስርዓት ሽግግርን ውጤታማ ለማድረግ ከአስተሳሰብ ጀምሮ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የምግብ ስርዓት ሽግግርና ኒውትሪሽን ፍኖተ-ካርታ ትግበራ መዘጋጀቱ በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ ወሳኝ ነው ያሉት አቶ ጌታሁን፣ ባለድርሻ ተቋማት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በግብርናው ዘርፍ ትልቅ አቅም ያለበት በመሆኑ ይህንን ምቹ አቅም በጋራ ማልማትና መጠቀም ይገባል ብለዋል።
የምግብ ስርዓት ሁሉንም የሚመለከት ነው ያሉት አቶ ጌታሁን፣ መቀንጨርን በመከላከል ጤነኛ እና አምራች ዜጋ ለማፍራት የባለድርሻ አካላትን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
#የቤኒሻንጉል_ጉሙዝ_ክልል_የመንግሥት_ኮሙኒኬሽን_ጉዳዮች
