ያለፉት ሶስት ዓመታት ፈታኝ የሁለተኛው የጤና ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የትግበራ ሂደት እና የህብረተሰቡን ጤናና ደህንነት ወደ ተሸለ ደረጃ ለማድረስ ለተካሄደውና ለተገኝው አመርቂ ውጤት ምስጋናዬንና የተሰማኝን ደስታ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ የጤና አገልግሎት ተደራሽትን በማሳደግ ዋና ዋና ተላላፊ በሽታዎችን በመዋጋት ረገድ ተጨባጭ እርምጃ የተወሰደ በመሆኑ የዜጎች በህይወት የመኖር ምጣኔ ተሸሽሏል፤ የሞት ምጣኔ ቀንሷል እንዲሁም የእናቶችና ህፃናት ጤናን በማሻሻል ረገድ ተጨባጭ ለውጥ በማስመዝገባችን በርካታ ውድ ህይወት ማትረፍ ችለናል፡
የተገኙትን ውጤቶች ከማክበር ባለፈ ክልሉ ያጋጠመውን ተግዳሮቶችንም ማስታወሱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ክልሉ ካጋጠመው የውስጥ ግጭት ለበርካታ ህብረተሰብ መፈናቀል፣ ለጤና ተቋማት ውድመት፣ ለህክምና ግብዓቶች ስርጭት መቋረጥ እና ለበርካታ ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፡፡
የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ እና ሌሎች ድንገተኛ የሆኑ የወረርሽኝ በሽታዎች ለጤና ሥርዓታችን ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብናል፤ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በጥረት የተገኘውን ውጤት ወደ ኋላ መልሶብናል፡፡ ተላላፊ በሽታዎች፣ እየጨመረ የመጣው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ክስተት እና የጉዳት አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት የተለየ ስልት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ክስተት እና የአካል ጉዳት አደጋዎች እየጨመረ መምጣት በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፡፡ አካባቢያዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልዩነቶችም የአገልግሎት ተጠቃሚነትና ውጤቱ የበለጠ እንዲወሳሰብ አድርጎታል፡፡ እንዲሁም ከምንፈለገው የጤና ግብ ለመድረስና ጥራት ያለው የጤና አገልግለት ላይ ለመድረስ የማያቋርጥ ማሻሻያ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
የወቅቱን ተለዋዋጭ ሁኔታዎች እና ላቅ ያለ ጠቀሜታውን ከግንዛቤ በማስገባት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት (2016-2018 በጀት ዓመት) ሥራ ላይ የሚውል የመካከለኛ ዘመን የጤና ዘርፍ ልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ የዚህ ዕቅድ ትኩረት ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ሽፋንን በማሳደግ፣ ለጤና አደጋዎች ምላሽ አሰጣጣችንን በማጎልበት፣ ሀገራዊ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓታችንን በማሻሻል እና የጤና አገልግሎት ሥርዓት ምላሽ ሰጪነትን በማሳደግ አጠቃላይ የማህበረሰብ ጤና ሁኔታ ከፍ ማድረግ ነው፡፡
