የቢሮ ኃላፊ መልዕክት

የቢሮ ኃላፊ መልዕክት

ያለፉት ሶስት ዓመታት ፈታኝ የሁለተኛው የጤና ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የትግበራ ሂደት እና የህብረተሰቡን ጤናና ደህንነት ወደ ተሸለ ደረጃ ለማድረስ ለተካሄደውና ለተገኝው አመርቂ ውጤት ምስጋናዬንና የተሰማኝን ደስታ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ የጤና አገልግሎት ተደራሽትን በማሳደግ ዋና ዋና ተላላፊ በሽታዎችን በመዋጋት ረገድ ተጨባጭ እርምጃ የተወሰደ በመሆኑ የዜጎች በህይወት የመኖር ምጣኔ ተሸሽሏል፤ የሞት ምጣኔ ቀንሷል እንዲሁም የእናቶችና ህፃናት ጤናን በማሻሻል ረገድ ተጨባጭ ለውጥ በማስመዝገባችን በርካታ ውድ ህይወት ማትረፍ ችለናል፡

 

የተገኙትን ውጤቶች ከማክበር ባለፈ ክልሉ  ያጋጠመውን  ተግዳሮቶችንም ማስታወሱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ክልሉ ካጋጠመው  የውስጥ ግጭት ለበርካታ ህብረተሰብ መፈናቀል፣ ለጤና ተቋማት ውድመት፣ ለህክምና ግብዓቶች ስርጭት መቋረጥ እና ለበርካታ ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፡፡

የኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ እና ሌሎች ድንገተኛ የሆኑ የወረርሽኝ በሽታዎች ለጤና ሥርዓታችን ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብናል፤ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በጥረት የተገኘውን ውጤት ወደ ኋላ መልሶብናል፡፡ ተላላፊ በሽታዎች፣ እየጨመረ የመጣው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ክስተት እና የጉዳት አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት የተለየ ስልት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ክስተት እና የአካል ጉዳት አደጋዎች እየጨመረ መምጣት በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል፡፡ አካባቢያዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልዩነቶችም የአገልግሎት ተጠቃሚነትና ውጤቱ የበለጠ እንዲወሳሰብ አድርጎታል፡፡ እንዲሁም ከምንፈለገው የጤና ግብ ለመድረስና ጥራት ያለው የጤና አገልግለት ላይ ለመድረስ የማያቋርጥ ማሻሻያ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

 

የወቅቱን ተለዋዋጭ ሁኔታዎች እና ላቅ ያለ ጠቀሜታውን ከግንዛቤ በማስገባት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት (2016-2018 በጀት ዓመት) ሥራ ላይ የሚውል የመካከለኛ ዘመን የጤና ዘርፍ ልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡ የዚህ ዕቅድ ትኩረት ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ሽፋንን በማሳደግ፣ ለጤና አደጋዎች ምላሽ አሰጣጣችንን በማጎልበት፣ ሀገራዊ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓታችንን በማሻሻል እና የጤና አገልግሎት ሥርዓት ምላሽ ሰጪነትን በማሳደግ አጠቃላይ የማህበረሰብ ጤና ሁኔታ ከፍ ማድረግ ነው፡፡

 

የጤና ዘርፍ የመካከለኛ ዘመን ልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ከሀገራዊ የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ጋር በማጣጣም በዘርፉ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አቀራረብ ላይ ከዚህ ቀደም ሲሰራበት ከነበረው የአምስት ዓመት ዕቅድ አሰራር ላይ በልዩነት ለውጥ ማምጣቱን ተመልክተናል፡፡ ይህንን ለውጥ መቀበላችን ባለፉት ሦስት ዓመታት ያጋጠሙንና መለየት ያልቻልናቸውን ውስብስብ ችግሮች ለማየት ዕድል ሰጥቶናል፡፡

 

በዕቅዱ የተቀመጡት ዘጠኝ ስትራቴጂክ ዓላማዎች ለዚህ የለውጥ ጊዜ የተቀመጡትን የትኩረት መስኮች ግልጽ አድርጓል፡፡ ቅድሚያ የተሰጣቸው ቁልፍ ተግባራት የሥነ-ተዋልዶ፣ የእናቶች፣ የጨቅላ ህፃናት፣ የህፃናት፣ የአፍላ ወጣቶች እና የወጣቶች ጤናን የሚያጠቃልል ሲሆን እንደ ኤች አይ ቪ፣ ቲቢ እና ወባን የመሳሰሉ ዋና ዋና ተላላፊ በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር ቀጣይነት ያላቸው ተግባራት ናቸው፡፡ በተጨማሪም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እና የአዕምሮ ጤና ህመሞች በመጀመሪያ የጤና አገልግሎት አሃድ ውስጥ በተቀናጀ ስልት ትኩረት ተሰጥቶ እንዲተገበር ወሳኝ ተግባር ሆኖ ተካቷል፡፡

 

የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የስትራተጂያችን ማዕከል እንደመሆኑ ፕሮግራሙ አዲስ በተከለሰው ፍኖተ ካርታ ውስጥ ከፍ ብሎ መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን በማስፋት ለሁሉም ተደራሽ የሚሆንበት ግብ እንዲኖረው ተደጓል፡፡ ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ሲያጋጥሙ የህዘባችንን ደህንነት ለመጠበቅ ከምነግዜውም በላይ ቁርጠኛነታችን የማይናወጥ ነው፡፡

 

ለማንኛውም የአደጋ ክስተቶች ምላሽ መስጠት የሚችል ጠንካራ የህብረተሰብ ጤና የድንገተኛ አደጋዎች የአሰተዳደር ሥርዓት እና የማይበገር የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ግንባታን በማጠናከር ላይ እንገኛለን፡፡ ይህም በጤና አገልግሎት አሰጣጥ፣ በአመራርና አስተዳደር፣ በህክምና ግብዓቶች አቅርቦት፣ የጤና መረጃ ሥርዓትን ማሳደግ፣ የጤና ባለሙያዎቻችን ማብቃት፣ የጤና ተቋማቶቻችን አቅም ማሳደግ፣ የዲጂታል ጤና ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ማዋል እና የጤና አጠባበቅ ፈጠራዎችን ማበረታታትን ይጨምራል፡፡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች በጤና ውጤቶቻችን ላይ የሚያሳድሩትን ጥልቅ ተፅእኖዎችን በመገንዘብ፣ ከሌሎች ዘርፎች ጋር የሚኖረንን ትብብር በማጠናከር እነዚህን ምክንያቶች በብቃት ማስቀረት ያስፈልጋል፡፡ የግሉን ዘርፍ ተቋማት ስትራቴጂያዊ በሆነ መልኩ በማሳተፍ ለግቦቻችን ዕውን መሆን የድርሻቸውን ጉልህ ሚና እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

 

በመጨረሻም በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ የማቋቋም፣ የህክምና ቁሳቁሶችና መሣሪያዎችን አቅርቦት ማሳደግ፣ የግሉ ዘርፍ በጤና ዘርፍ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ማበረታታት እና የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ማሳደግ፣ የጤና መሰረተ ልማት ችግሮችን መፍታት፣ የሰው ሀብት ልማት እና የቁጥጥር ሥርዓት ማጠናከር የቀጣይ ሦስት ዓመታት በጤናው ዘርፍ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጣቸው ቁልፍ ሥራዎቻችን ናቸው፡፡ በጠንካራ ቁርጠኝነት እና ትብብር የጤና ዘርፍ የመካከለኛ ዘመን የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅዳችን ጤናማ አምራችና  የበለፀገ ማህብረሰብ  የምናረጋግጥበት ትክክለኛ መንገድ እንደሚሆን እምነቴ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *