Image

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ

Benishangul Gumuz Regional State Health Bureau

የጤና ባለሙያዎች ዉይይት

የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ከጤና ባለሙያዎች የተነሱ የመብት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች በሚነሱ የተሳሳቱ አሉባልታዎች ሳይረበሹ መደበኛ ሥራዎችን በተለመደዉ መልኩ እያከናወኑ መሆኑን የፌዴራል ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የጤና ሚ/ር ተወካይ ወ/ሮ ላምሮት አንዱዓለም ገለፁ ። ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ በአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል ያለዉን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ ከሆስፒታሉ የማኔጅመንት አባላት ጋር መክረዋል ። የፌዴራል ጤና መድህን አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ላምሮት አንዱአለም የሆስፒታሉን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውሮ ከተመለከቱ በኋላ የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች በጤና ባለሙያዎች የተነሱ የጥቅማ ጥቅምና የመብት ጥያቄዎች ጋር ተያይዞ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የጤና ባለሙያዎች ሥራ እንዳቆሙ ተብሎ በሚተላለፉ አሉባልታዎች ሳይሸበሩ በተገቢው ሁኔታ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው ገልጸዋል ። በጤና ባለሙያዎች የተነሱ የጥቅማ ጥቅም እና የመብት ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸውና መመለስ ያለባቸው መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ ያምሮት ጥያቄዎቹ ምላሽ እስኪ ያገኙ ድረስ ባለሙያዎቹ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ ምላሹን መጠባበቅ እንደአለባቸዉ አስገንዝበዋል ። ከተነሱ የጥቅማ ጥቅምና የመብት ጥያቄዎች መካከል በሆስፒታሉ በራሱ መፈታት በሚገባቸው ጉዳዮች ጋር ከሆስፒታሉ የማኔጅመንት አባላት ጋር ዉይይት ተደርጎ በሆስፒታሉ አቅም መፈታት የሚገባቸው ችግሮች በአጭር ጊዜ ዉስጥ መፈታት እንዳለበትም ወ/ሮ ያምሮት ገልፀው ከሆስፒታሉ አቅም በላይ የሆኑ ጥያቄዎች በጤና ቢሮ፣በክልሉ መንግስትና በፌዴራል መንግስት ይፈታሉ ብለዋል። የአሶሳ ሆስፒታል የማኔጅመንት አባላትም በሆስፒታሉ መፈታት የሚገባቸውን የጥቅም ጥቅም ጥያቄዎች በተለይም የትርፍ ጊዜ ክፍያና የደንብ ልብስ ጥያቄ ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀው ችግሮቹን በዘለቄታዊነት ለመፍታት ከመንግሥት ለግዴታ ወጪዎች በቂ በጀት መመደብ እንደአለበት ጠይቀዋል ። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ የፕሮግራም ዘርፍ ምክትል የቢሮ ሀላፊ አቶ አብዱልሙኒየም አልበሽር በበኩላቸው ከሆስፒታሉ አቅም በላይ የሆኑ ችግሮችን በቢሮ ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግና ከቢሮ አቅም በላይ የሆኑ ችግሮችን ለሚመለከታቸው አካላት ቀርቦ እልባት እንደሚሰጥ ገልፀው ሆስፒታሉ ከመንግሥት የሚመደብለትን በጀትና የዉስጥ ገቢ የሚሰበስበዉን በጀት በትክክል ለታለመለት አላማ ማዋል እንዳለበትም አሳስበዋል ። ግንቦት 13/2017 ዓ.ም