Image

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ

Benishangul Gumuz Regional State Health Bureau

የባለሙያዎች ዉይይት

የጤና ባለሙያዎች በሀገራዊ እድገት ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ዘርፉን በተደራጀ መልኩ መደገፍ ይገባል ************* የጤና ባለሙያዎች በሀገራዊ እድገት ላይ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ዘርፉን በተደራጀ መልኩ መደገፍ እንደሚገባ ተገለጸ። የክልልና የዞን አመራሮች ''የጤናው ዘርፍ አርበኝነት ለሀገር እድገት'' በሚል መሪ ቃል ከፓዊ ሆስፒታልና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሰራተኞች ጋር በፓዊ ከተማ ውይይት አካሂደዋል። የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት ሽቱ፤ የጤና ባለሙያዎች የተሰጣቸው ሰውን የማዳን ሃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸው ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ሀገር ከሚያፈርሱ ሃይሎች አጀንዳ መጽዳት እንደሚገባ ገልጸዋል። ለሀገር እድገትና ብልጽግና የጤናው ዘርፍ ባለሙያዎች ወሳኝ በመሆኑ ዜጎችን ስነ ምግባር በተሞላበት መልኩ በማገልገል ሙያዊ ግዴታን በመወጣት የተጀመሩ ግቦች ማሳካት አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ወልተጂ በጋሎ፤ የባለሙያዎች መሰረታዊ ጥያቄ በሙያ ማህበራት በኩል በተደረጃ መልኩ ማቅረብ ሲቻል ሰላምና መረጋጋትን በማይፈልጉ ሃይሎች የአጀንዳ ማስፈጸሚያ እየተደረገ በመሆኑ በትኩረት ማየት እንደሚገባ ገልጸዋል። እንደ ሀገር እየተጸባረቀ ያለው የዘርፉ ባለሙያዎች ጥያቄ አስፈላጊ ቢሆንም ሀገራዊ ሁኔታን ያገናዘበና ግምት ውስጥ በማስገባት ሊሆን ጭምር እንደሚገባ ገልጸዋል። መንግስት በዘርፉ በየደረጃው የሚነሱ ጥያቄዎችን እንደ ሀገር እስከ ምን ድረስ ማድረግ እንደሚችል በመለየት በህግና መመሪያ ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን አክለው ገልጸዋል። የስብሰባ ተሳታፊዎች ከሙያና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ጋር በተያያዘ ላነሱት ጥያቄም በየደረጃው በሚመለከታቸው አካላት በኩል በሂደት ምላሽ እንደሚሰጥ መገለጹን የመተከል ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ ዘገባን ጠቅሶ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ዘግበዋል።