Image

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ

Benishangul Gumuz Regional State Health Bureau

የመረጃ ሥርዓት

በመተከል ዞን የጤና መረጃ ሥርዓት በማጠናከር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ። (ሚያዝያ 26/2017ዓ.ም) ቢሮው ባለፉት የ9 ወር የተከናወኑ የጤና የመረጃ ሥርዓት የስራ አፈፃፀም በግልገል በለስ ከተማ ግምገማ አካሂዷል።፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ የኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ አለም ደበሎ በሪፖርት ግምገማ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት የጤና መረጃ ስርአት አንዱ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ነው በማለት ይህ የመረጃ ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉ ከቢሮ ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ወጥ የሆነና የተናበበ የመረጃ ሥርዓት እንዲፈጠር ያደርጋል ሲል ተናግረዋል ። የጤና መረጃ ሥርዓትን በማጠናከር በጤና ተቋማት የሚሰጠው የጤና አገልግሎት ጥራት እንዲሻሻል ለሁሉም HMIS ባለሙያዋች ከዚህ በፊት ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል። እንደ አቶ አለም አገላለፅ የጤናው ዘርፍ መረጃ ስርዓት ከሌሎች ተቋማት የተለየ መሆኑን በመግለፅ የመረጃ ስርአቱ ከጤና ሚ/ር እስከ ጤና ኬላ በተዋረድ የተዘረጋ በመሆኑ በማንኛውም ደረጃ ያለን የጤና መረጃ በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችል ነው ብለዋል። ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክለው የጤና መረጃ ሥርዓትን በተገቢዉ ሁኔታ አለመያዝ ከበጀት አመት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ በጀት አመት ማብቂያ ድረስ ዘርፈ ብዙ ስራዎች የሚከናወኑ ቢሆንም በመረጃ አያያዝ ድክመት አመቱን ሙሉ የተሰሩ ስራዎችና የተለፉ ልፋቶች ዋጋ በማሳጣት አፈፃፀማችን እንዲወርድ የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል። የጤና መረጃ ሥርዓትን የተሳለጠ ለማድረግ ከላይ እስከታችኛዉ መዋቅር የተናበበና መግባባት ላይ የተደረሰ እቅድ ዝግጅትና ሪፖርትን ልዉዉጥ መኖር እንደአለበት ያስገነዘቡት ም/ ኃላፊዉ መረጃ ለአንድ ተቋም ህያውነት መረጋገጥ መሠረታዊ ነገር በመሆኑ አመራሮች ሪፖርት በአግባቡ መገምገም እንዳለባቸዉ አሳስበዋል። የመተከል ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ታረቀኝ አርገታ በበኩላቸው የዘጠኝ ወር የጤና መረጃ ስርዓት አፈፃፀም ግምገማ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ወረዳዎች በዳታ አገባብ ዙሪያ ያለባቸውን ክፍተቶች በመለየት በቀጣይ የተከናወኑ ተግባራት ወደ መረጃ ስርዓት የማስገባት ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተዉ በመስራት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ለማስቻል ነው ብለዋል። በተለይ የጤና መረጃ ሥርዓትን የማጠናከር፣ለጤና መረጃ ሥርዓት የሚዉሉ ግብዓቶችን በማሟላት፣በአቅም ግንባታ ሥራዎች የተከናወኑ ተግባራት ተጠቃሽ መሆናቸውን ዶ/ር ታረቀኝ ገልፀዋል ። የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የማቴሪያል እጥረት፣ በየወቅቱ መረጃዎችን ያለመናበብና ያለመገምገም፣ባለሙያዎች በቅንጅት ያለመስራት እና የኢንተርኔት ተደራሽነት ችግር መኖሩን በግምገማው ወቅት ተናግረዋል ። በመድረኩ ላይ የመተከል ዞን ሁሉም ወረዳዎች እና የቢሮው የ9 ወር የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ዉይይት ተደርጎበታል።