Image

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ

Benishangul Gumuz Regional State Health Bureau

የጤና ኤክሰቴንሽን የ9 ወር የአፈፃፀም ግምገማ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን በባለፉት 9 ወር በጤናዉ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸው ተገለፀ ። (ሚያዝያ 25/2017 ዓ.ም ) ቢሮው በመተከል ዞን በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ የስራ አፈጻጸም ሪፖርቶችን በግልገል በለስ ከተማ ተገምግሟል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አለም ደበሎ በሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ እንዳሉት በክልሉ በባለፉት ዘጠኝ ወራት ለዞኑ ማህበረሰብ ቀልጣፋና ጥራት ያለዉ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸዉን ተናግረዋል ። በጤናው ዘርፍ ለውጥ ለማስመዝገብ የተቀመጡ የትኩረት አቅጣጫዎችን ግብ ለመምታት የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስፋት ረገድ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አክለው ገልጸዋል። በሁሉም ወረዳዎች ከሜዳ መፀዳዳት ነፃ የሆነ ቀበሌ፣ የንፁህ መጠጥ ወሃ እና የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ላይ ትኩረት አደርጎ እንዲሰራ አቶ አለም ደበሎ አሳስበዋል ። ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወነው የስራ አፈጻጸም የታዩ ጠንካራ ጎኖችን በማጠናከርና የነበሩ ክፍተቶችን በዕቅድ በማካተት በቀጣይ ትኩረት በመስጠት ከታቸኛው አመራር ጋር በመቀናጀት መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል ። የመተከል ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ ዶ/ር ታረቀኝ አርገታ በበኩላቸው የዜጎችን ጤና በዘላቂነት ለመጠበቅ በሁሉም ዘርፍ የታዩ ክፍተቶችን በማስተካከል ሁሉም የወረዳ ባለድርሻ አካላትና ባለሙያዎች በጋራ በመቀናጀት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል። በአንድአንድ ወረዳዎች በተለይ የDHIS2 ሪፖርተር ችግር ፣ ሪፖርት በወቅቱ የማቅረብ ችግር ፣ የባለሙያዎች የተነሳሽነት ችግር ፣ የተሽከርካሪ እጥረት ፣የበጀት እጥረት እና የመሰረታዊ የመፀዳጃ ቤት ቁጥርን ከማሻሻል አንፃር ችግሮች እንዳሉ ሪፖርቱ ማመላከቱን ጠቁመዋል ። የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው መረጃዎች በተገቢው መንገድ በጊዜ ለባለድርሻ አካላት ያለመድረስ ክፍተት እና የግባዓት እጥረት እንዳለ ተናግሮ ለወደፊቱ በመቀናጀት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል ።. ተሳታፊዎቹ አክለው ለጤናው ዘርፍ አፈፃፃም የባለሙያዎች ተረጋግቶ ያለመስራት፣ የተሸከርካሪ ችግር ፣ የበጀት እጥረት ተግዳሮት እንደሆነባቸው አንስተዋል ። እንዳጠቃላይ ባለፉት 9 ወራት በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ ጠንካራ ጎኖችን ማስቀጠልና የታዩ ድክመቶችን የቀጣይ የዕቅድ አካል አድርገው እንዲሰሩ ቢሮ ለላፊው አሳስበዋል። በግልገል በለስ ከተማ በተደረገው የዘጠኝ ወር የጤናው ዘርፍ ግምገማ የክልል፣የዞንና የወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊዎች ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።