Image

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ

Benishangul Gumuz Regional State Health Bureau

የቤተሰብ ዕቅድ የንቅናቄ መድረክ

የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማሻሻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለበት የመተከል ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አሳሰቡ። (23/8/2017 ዓ.ም) የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቤተሰብ ዕቅድ ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ተካሄዷል ። የመተከል ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ፍቃዱ ደበሎ የንቅናቄ መድረኩን በከፈቱበት እንደአሉት የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚነትለማሻሻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳአለባቸዉ ነዉ። የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚነትን ማሻሻያ ለጤና መዋቅሮች ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ከሀይማኖት አባቶች ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የህብረተሰቡን ንቃተ ህልና በማሳደግ የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚነትን ለማሻሻል በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ምክትል አስተዳዳሪዉ። የመተከልዞን ብልፅግና ፖርቲ ቅርንጫ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ደበል በልጋፎ ከቤተሰብ ዕቅድ አጠቃቀም መሻሻል በየአካባቢውና በተለያዩ የእምነት ተቋማት ላይ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለመቅረፍ በቅንጅት መሰራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል ። በንቅናቄ መድረክ የተፈጠረውን ግንዛቤ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም እስከታችኛው መዋቅር ማውረድ እንደአለባቸዉ አቶ ደበል ገልጸዋል ። የመተከል ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ ዶ/ር ታሬቀኝ አርገታ በበኩላቸው 40 በመቶ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የጎላ ድርሻ ያለዉን የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚነትን ከማሻሻልና ከማጠናከር አኳያ በየጤና ተቋማቱ የተከናወኑ ተግባራትና የተመዘገቡ ዉጤቶች በተፈለገው መልኩ ባለመሆኑ የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ለመጨመር የንቅናቄ መድረክ መዘጋጀቱን ገልጸዋል ። በተለይም የወጣቶች ስነ ተዋልዶ ጤና የማሻሻል፣ያለዕድሜ ጋብቻና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን የማስቀረት ተግባራት ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ በመሆኑን ዶ/ር ታሬቀኝ ገልፀዋል። በክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶችና ወጣቶች ጤና  አገልግሎት ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ አየሩ ጌትነት ባቀረቡት ሠነድ የቤተሰብ ዕቅድ  አገልግሎት እና የአፍላ ወጣቶች  እና የወጣቶች ጤና አገልግሎት  አፈፃፀም መሻሻል እንዳለበት ጠቅሰው በወጣትነት ዕድሜ የሚከሰቱ እርግዝናን ከመቀነስ አኳያ የሚታየው አፈፃፀም ዝቅተኛ ነዉ ብለዋል። አቶ አየሩ አክለውም በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ዙሪያ የሚሰሩ የተግባቦትና ግንዛቤ ስራዎች የተጠቃሚዎችን ፍላጎትና ምርጫ ከግምት ያስገባ መሆን እንዳለበት ተናግሯል። በንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙ የሀይማኖት አባቶች የቤተሰብ ዕቅድ መጠቀም ምንም አይነት ሀይማኖታዊ ዳራ የለለው መሆኑን ገልፀው በጤና ተቋማት አከባቢ የሚሰጠው የጤና አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል አለበት ብለዋል። በንቅናቄ መድረኩ ላይ የሀይማኖት አባቶች፣ የሴቶችና የወጣቶች ተወካዮች፣የዞንና የወረዳ ጤና ጽ/ቤትና የጤና ጣቢያ ሀላፊዎችና የሆስፒታል ሥራ አስከያጆች ተገኝተዋል ።