Image

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ

Benishangul Gumuz Regional State Health Bureau

የጤና ኤክሰቴንሽን የተሀዲሶ ስልጠና

የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ሥራን ለማሳለጥ ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የተሀዲሶ ስልጠና መስጠት ወሳኝ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ ገለፀ ። (20/8/2017ዓ.ም) ለ10 ተከታታይ ቀናት የሚሰጥ የጤና ኤክስቴንሽን የተሀድሶ ስልጠና በግልገል በለስ ከተማ ተጀምሯል ። የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ለማጠናከር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል በተለያዩ የጤና ፕሮግራሞች ላይ የተሀድሶ ስልጠና መስጠት አንዱ ነው ። በዚሁ መሠረት ከመተከል ዞን 4 ወረዳዎች ለተወጣጡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በግልገል በለስ ከተማ የተቀናጀ የተሀድሶ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል ። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ የመሠረታዊ ጤና አገልግሎት እና የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ክብሩ ሰባኒ የስልጠናው ዋና ዓላማ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አቅም ለመገንባት እና ከአዳዲስና ከወቅታዊ የጤና ፕሮግራሞች ጋር ለማስተዋወቅ መሆኑን ገልጸዋል ። ይህ ስልጠና የክህሎት ስልጠና በመሆኑ ሰልጣኞች ስልጠናውን በተገቢው ሁኔታ መከታተል እንደአለባቸዉ አሳስበዋል ። በቢሮው የጤና ኤክሰቴንሽን ፕሮግራም ባለሙያ አቶ መስፍን ተሾመ በበኩላቸው የተሀድሶ ስልጠና በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች ሲሰጥ የቆየ መሆኑን ገልፀው በዚህኛው ዙር በተላላፊ በሽታዎች ፣ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች፣በቲቢና ሥጋ ደዌ፣ ትኩረት በሚሹ ሀሩራማ በሽታዎችና በወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ስልጠናዎች እንደሚሰጥ ተናግሯል ። በስልጠናው ላይ ከ4 ወረዳዎች የተወጣጡ 179 የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና 12 የጤና ኤክስቴንሽን ሱፐርቫይዘሮች መሳተፋቸውን አቶ መስፍን ገልጸዋል ።