Image

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ

Benishangul Gumuz Regional State Health Bureau

የግብዓት ድጋፍ ተደረገ

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር በፓዊ ወረዳ ፈለገ ሰላም ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ለእናቶች ማቆያ ክፍል አገልግሎት የሚውል ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ። ማህበሩ ከUNFPA ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በፓዊ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ለፈለገ ሰላም ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚገመት የተለያዩ መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል። የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ቀልቤሳ ተሬሳ፥ ማህበሩ በክልሉ በስድስት ወረዳዎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፥ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው መስኮች በግጭትና ተያያዥ ችግሮች ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ጥራት ያለው የእናቶችና ህፃናት አገልግሎት መስጠት፣ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች መቅጠርና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን መስጠት መሆኑን ገልጸዋል። ማህበሩ በፈለገ ሰላም ጤና አጠባበቅ ጣቢያ የእናቶች ማቆያ ክፍል ምቹ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል በግማሽ ሚሊዮን ብር በሚገመት ወጪ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አቶ ቀልቤሳ ጨምረው ገልፀዋል። የመተከል ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ታረቀኝ አርጋታ እንደገለፁት ደግሞ፥ ወላድ እናቶች ወደ ጤና ተቋማት ሲመጡ እንደቤታቸው በመቁጠር በቆይታቸው ጤናማና ደስተኛ ሆነው እንዲመለሱ ለማስቻል ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። የፓዊ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ሎዳሞ፥ የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ከUNFPA ጋር በመተባበር ያበረከተው ድጋፍ ህክምናው ለማሳለጥ ወሳኝ በመሆኑ ንብረቱን በአግባቡ በመያዝ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል ብለዋል። ማህበሩ በክልሉ ውስጥ የእናቶችና ህጻናትን ጤና በዘላቂነት ለመጠበቅ በጤና ተቋማት ላይ የቁሳቁስ ዕጥረትን ከመቅረፍ ባለፈ እናቶች በሰለጠነ ባለሙያ እንዲወልዱ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የመተከል ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ ዘግቧል።