Image

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ

Benishangul Gumuz Regional State Health Bureau

የጤና መረጃ ሥርዓት

የጤና መረጃ ሥርዓት  በማጠናከር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ  የሁሉም ባለድርሻ  አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ መሆኑን  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ ። (18/9/2017ዓ.ም)ቢሮው ባለፉት የ9 ወር የተከናወኑ የጤና የመረጃ ሥርዓት  የስራ  አፈፃፀም ግምገማ  አካሂዷል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ወልተጂ በጋሎ  በሪፖርት ግምገማ  መክፈቻ ላይ  እንደተናገሩት  የጤና መረጃ ስርአት  አንዱ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ነው በማለት ቀደም ሲል  የነበረው የጤና የመረጃ ስርዓት   HMIS  በኛ ባለመበልፀጉ  በቀላሉ  ለጉዳት በመዳረጉ ከ2010ዓ/ም ጀምሮ DHS2 የማበልፀግ ስራ በመስራት ወደ ትግበራ የተገባ ሲሆን በሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድ   በጤና   የመረጃ ስርዓቱ ላይ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ  ችግሮች  በሂደት እየተቀረፉ  ወደ ተሻለ ደረጃ  ማድረስ መቻሉን  ሀላፊዉ ገልፀዋል። እንደ አቶ ወልተጂ አገላለፅ  የጤናው ዘርፍ  መረጃ ስርዓት ከሌሎች ተቋማት  የተለየ መሆኑን በመግለፅ የመረጃ ስርአቱ ከጤና ሚ/ር እስከ   ጤና  ኬላ  በተዋረድ የተዘረጋ  በመሆኑ   በማንኛውም ደረጃ ያለን የጤና መረጃ  በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችል  ነው ብለዋል። ቢሮ ኃላፊው አክለው   የጤና መረጃ  ሥርዓትን   በተገቢዉ ሁኔታ አለመያዝ ከበጀት  አመት መጀመሪያ  ጀምሮ እስከ በጀት አመት ማብቂያ ድረስ ዘርፈ ብዙ ስራዎች  የሚከናወኑ  ቢሆንም በመረጃ አያያዝ ድክመት አመቱን ሙሉ የተሰሩ ስራዎችና የተለፉ ልፋቶች  ዋጋ በማሳጣት  አፈፃፀማችን  እንዲወርድ የራሱን  አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለዋል።   የጤና መረጃ ሥርዓትን  የተሳለጠ ለማድረግ ከላይ እስከታችኛዉ መዋቅር የተናበበና መግባባት ላይ የተደረሰ እቅድ ዝግጅትና  ሪፖርትን ልዉዉጥ  መኖር እንደአለበት  ያስገነዘቡት ሀላፊዉ  መረጃ ለአንድን ተቋም ህያውነት መረጋገጥ  መሠረታዊ ነገር  በመሆኑ  አመራሮች ሪፖርት  በአግባቡ መገምገም  እንዳለባቸዉ አሳስበዋል። በጤና ቢሮ የኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ አለም ደበሎ በበኩላቸው  የዘጠኝ ወር የጤና መረጃ ስርዓት  አፈፃፀም  ግምገማ  ያስፈለገበት ዋና ምክንያት  ወረዳዎች  በዳታ አገባብ  ዙሪያ ያለባቸውን ክፍተቶች በመለየት  በቀጣይ የተከናወኑ ተግባራት  ወደ መረጃ ስርዓት  የማስገባት  ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተዉ በመስራት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ለማስቻል ነው ብለዋል። በመድረኩ ላይ  የአሶሳ ዞን ሁሉም ወረዳዎች: የማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ  እንዲሁም የቢሮው የ9 ወር የአፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ  ዉይይት ተደርጎበታል።